14/01/2025
ሎስአንጀለስን ሞቅናት! (በእውቀቱ ስዩም)
ትናንትና ሎስአንጀለስ በእሳት ስትነድ፥ እኔ በአጋጣሚ ጓደኞቼን ለመሰናበት እዚያው ከተማ ውስጥ ነበርሁ፤ ሆሊውድ አካባቢ በእግሬ እየተንሸራሸርሁ ድንገት ቀና ብየ ሳይ፥ ከተማው እንደ ደመራ ይንቦገቦጋል፤ መጀመርያ ላይ ፥የዮዲት ጉዲትን ፊልም እየሰሩ ነበር የመሰለኝ፤ ብዙ ሳይቆይ የሳት አደጋ መኪና እየተብለጨለጨ ባጠገቤ አለፈ፤
ነገሩ “ሲርየስ” መሆኑን ያወቅሁት፥ የሆሊውድ አክተሮች ልጆቻቸውን እንኮኮ አዝለው፥ የቤት እቃቸውን ባንሶላ ጠቅልለው፥ ሲራወጡ ስመለከት ነው ፤ ደንብ አስከባሪ የሚያባርራቸውን የመገናኛ ቦንዳ ሻጮችን አስታወሱኝ፤ ቻክኖሪስ ባንድ የእሳት አደጋ ሰራተኛ ታዝሎ፥ ሳል እያጣደፈው ከቤቱ ሲወጣ አይቼ “እድሜ አተላ “ብየ ተከዝኩ::
እያወካ እየተጋፋ ከሚሸሸው ሰው መሀል ተቀላቅየ መሮጥ ጀመርሁ፤
ቀጣዩ ፌርማታ ላይ ትንፋሽ ለመሰብሰብ ቁጭ ባልሁበት፥ የሆነ ፖሊስ መጣና፤
“Are you ok?” አለኝ፤
“ እድሜ ልኬን ለፍቼ፥ እቁብ ጥየ ፥ ያፈራሁት ቤቴና ንብረቴ በእሳት ጋየ” ብየ መለስኩለት፤
“ስራህ ምንድነው ?”
መቸም በዚህ ሰአት ላይ ሊያጣራ አይችልም ብየ በማሰብ፥
“ ቀን የጣለኝ የሆሊውድ አክተር ነኝ “ አልሁት፤
“ምን ፊልም ላይ ሰርተሀል?”
”በማርቲን ሉተር ኪንግ የህይወት ታሪክ ዙርያ፥ በሚያጠነጥን ፊልም ውስጥ ከበድ ያለ ሚና ነበረኝ ” አልሁት፤
ፖሊሱ አልተፋታኝም፤
“ምን ሆነህ ነው የተወንከው?”
“ ማርቲን ሉተርኪንግ ፥ ሁለት መቶ ሺህ ህዝብ ሰብስቦ ንግግር የሚያደርግበት ትእይንት ትዝ ይለሀል?” አልኩት፤
“አዎ”
“ ከህዝቡ መሀል አንዱን ሆኜ ተውኛለሁ፤ ፊልሙ ጀምሮ አንድ ሰአት ከሶሰት ደቂቃ ከአምሳ ሁለት ሰከንድ ላይ ራሱን እሚነቀንቀው ሰውየ እኔ ነኝ “
ፖሊሱ ጥሩ ሰው ነው፤ ወስዶ ከተፈናቃዮች ጋራ ቀላቀለኝ፤ የከተማው ከንቲባ ዘለግ ያለ ንግግር አደረጉ ፤” የተወደዳችሁ ተፈናቃዮች ሆይ ! የከተማው አስተዳደር ቤታችሁን መልሶ እስኪገነባ ድረስ ባለ አምስት ኮከብ ሆቴል ውስጥ ልናቆያችሁ እንገደዳለን ”ብለው ንግግራቸውን አሳረጉ
፤
በመጨረሻ” የአደጋና ስጋት መስርያ ቤት” ሊቀመንበር ወደኔ ቀርቦ፥
“ የደረሰብህን ኪሳራ እስክናጣራ ፥ይቺን ነገር ላንዳንድ ነገር ትሁንህ “ አለና አምሳ ሺህ ዶላር የያዘች ትንሽ ብጫ ፌስታል አስጨበጠኝ፤
ብዙም ሳልቆይ፥ፌስቡኬ ላይ የሚከተለውን ማሳሰቢያ ጣል አረግሁ፤