28/03/2024
የአንድ ብዙ
የሥነ ምግባር ምሉዕነት ለረሱል (ሰዐወ) የተገባ ነው። አቡበከር ሲዲቅ ደግሞ የእሳቸው የቅርብ ሰው ናቸው። ረሱል (ሰዐወ) "ኢንነማ ቡዒስቱ ሊዑተሚመ መካሪመል አኽላቅ" ማለታቸውን ስናስብ የአንድ ሰውን ያህል በእርግጥ እኛ ሰምተን ታንጸናል ወይ? ብለን ራሳችንን እንድንጠይቅ ያደርገናል።
አንዳንድ ሰዎች አሉ ጆሯቸው ሰምቶ የማይሞላ፣ ሞልቶም የማያፈስ። ሁሉንም ዓይነት ድምጽ በጥሞና ሰምቶ ተገቢውን ምላሽ የመስጠት አቅም ያላቸው። እነሱን መሆን አይቻልም። እነሱን መሆን የሚችሉት እነሱ ብቻ ናቸው።
እያንዳንዱ ሰው የየራሱ መክሊት አለው። በጥበብ ሜዳ ላይ የሚጎን፣ በሃብት ሜዳ ላይ የሚገን፣ ለንግግር አንደበቱ ስል፣ ለፈጠራ ምናቡ ሩቅ፣ የሆነ ሰው አለ። እያንዳንዱ ሰው የየራሱ መክሊት አለው። ለአንዳንድ ሰው ደግሞ የተነባበረን አላህ ይሰጠዋል።
መከራን የሚቋቋም ትከሻ፣ ጡጫን የሚመክት ሰውነት፣ ግለምጫን የሚቋቋም ክብር፣ ችግርን የሚሻገር ጉልበት፣ አመራርነትን የተካነ ምጥቀት በአንድ ሰው ላይ ይታይ ይሆናል። የአንድ ብዙ።
በመልዕክተኛው የሥነምግባር አስተምህሮ ታንጾ በመጀመሪያው ኸሊፋ ምሉዕ ጠባይ ተኮትኩቶ ያደገ የዘመናችን ተምሳሌት ደግሞ መሐላችን አለ።
ትሕትና ሥጋ ለብሶ፣ ኃላፊነት ግዘፍ ነስቶ የሚታይበት የዘመናችን አርዓያ ሰብ። ነገሮች ቢያበሳጩት ውጦ፣ ንዴቱን ተቆጣጥሮ የዕለት ተግባሩን የዓመት ውጤቱን የሚያሰላ የትውልዱ አርዓያ ሰብ።
ሥነምግባርንም ከሲዲቅ ተውሷል። ባሕሪንም አስተምህሮንም ከረሱል ሰዐወ ድርሳነ ማኅደር አፍሷል። ይህ ሰው የዘመናችን ድንቅ ሆኖ ሳለ መሐላችን በመኖሩ አላወቅንለትም።
ከግለሰብ እስከ አገር ጉዳይ ይዞ ከቆላ ደጋ ሲባትል መች ይሆን የራሱን ሕይወት የሚኖር ያስብላል።
ትናንት መቀሌ ከነበር ነገ ሞያሌ ሊገኝ ይችላል፣ ጅግጅጋ ነው ሲሉት ባሌ ሮቤ ይታያል። ኢትዮጵያ ነው ሲሉት አሜሪካ፥ አሜሪካ ነው ሲሉት ዱባይ፣ ዱባይ ነው ሲሉት ካናዳ፣ ካናዳ ነው ሲሉት ቱርክ፣ ጣሊያን ፣ ጀርመን .... እሱ እዚህ ነው ብለው ሊደመድሙ አይችሉም። ይህ ሁሉ ታዲያ ለግል ጉዳዩ አይደለም።
አንዱ ጋ ሕዝቡን ከአላህ ጋር ያስታርቃል ፣ ሌላው ጋ የሕዝባችን ዋእይና ቸነፈር በዝቷልና እጃችሁን ወደኪሳችሁ ከትተታችሁ ሳትሰስቱ አምጡ ይላል። የሕዳሴው ግድብን ከእናንተ ውጪ የሚያጠናቅቀው የለም አምጡ፣ የኮረናን መከራ የምንቋቋመው በእናንተው ነው አምጡ እያለ አንድ ሆኖ ሺ ቦታ ይደርሳል። ኢትዮጵያ የዚህን ሰው ታላቅነት አለማወቋ የሚገርም ነው። በጎ ነው ብላ አልሸለመችው ደግ ነው ብላ አላወቀችው።
ቃል ሲገባ ካዝናው ውስጥ ያለውን አሟጦ ነው። ሲሰጥ ከነገውም ይበደራል። ምነዋ ቢሉ ከፊቱ የቆመው ችግር ውሎ የማያሳድር ይሆንበታል። ቢበዛልን የምንወደው ስናጣው የሚከፋን የዘመናችን ወደረኛ አልባ።
የእከሌ ወገን ተብሎ የማይመደብ፣ የቡድንተኝነት ማልያን የማያጠልቅ፣ ለተቸገሩ መሻኢኾች፣ ለተዘጉ ዛውያዎች፣ ለፈረሱ መሳጂዶች፣ ለወደቁ ስብእናዎች ሁሉ የሚጠራ የዘመኑ አርዓያ ሰብ። ችግር ባለበት ሁሉ አባ መፍትሔ።
መች ይሆን ለራሱ የሚኖረው? በሌሊት በኦንላይን ለአንዱ ተቋም ገቢ ሲያስብ ያገኙታል፥ በእኩል ቀን "ስንቅ ማጋራት" ሲያስተባብር ያዩታል። የጎዳና ወጣቶችን ለማብላት ይሮጣል፣ ችግኝ ለመትከል አፈር ይዝቃል። ሕመምተኞችን ሆስፒታል ሄዶ፣ ቁስለኞችን ግምባር ተገኝቶ ያጽናናል። ይህን ሰው ምን ብለን ብንገልጸው ይበቃው ይሆን?
የራሱ ሳይበቃ ቤተሰቦቹንም በራሱ መንገድ ያሰለፈ፣ ከሕመሙ ጋ ተናንቆ አደባባይ በአገር ጉዳይ፣ በዑማ ጉዳይ የሚጋፈጥ ምርጥ ሰብዕና።
የሕዝብ ድምጽ፣ የዑማው ልሳን፣ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጅ ማነው?
ዑስታዝ አቡበከር አሕመድ ሐላል ፕሮሞሽን በ4ኛው የጎዳና ላይ ኢፍጣር የኢትዮጵያ ኡስታዝ አቡበከር አህመድን የክብር እውቅና ይሸልማል።
ይህ ሽልማት የሕዝብ ነው። ሕዝብ ልጁን ያከብራል